የ2016 በጀት ዓመት የአስተዳደሩ ቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም

 የምዝገባ ምዝገባ ሽፋንን ለማሳደግ አስተዳደሩ ከሚሰራቸው ዋና ዋና ሥራዎች መካከል አንዱ የግል ድርጅቶችንና ሠራተኞቻቸውን በመመዝገብ የዐቅድ አባልነት ካርድ  መስጠት በመሆኑ በ2016 ዓ.ም 17,228 ድርጅቶችንና 149,843 ሠራተኞችን ለመመዝገብ ታቅዶ  18,747 ድርጅቶችንና 166,334 ሠራተኞችን መመዝገብ ተችሏል፡፡አፈጻጸሙ በድርጅት ምዝገባ 109 በመቶ ሲሆን በሠራተኛ ምዝገባ 111 በመቶ ነው፡፡

ይህ ከታቀደው በላይ መመዝገብ መቻሉ የሆነውም ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከባንኮች ጋር በተደረገው የቅንጅታዊ አሠራር ሥርዓት መፈጠር ነው፡፡ በበጀት ዓመቱም ለ18,394 ድርጅቶችና ለ163,245 ሠራተኞች የዐቅድ አባልነት ካርድ ተሰጥቷል ፡፡

የጡረታ ፈንዱን ለማዳበር የጡረታ መዋጮን አሟጦ መሰብሰብን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ብር 25.4 ቢሊዮን የጡረታ መዋጮ ለመሰብሰብ ታቅዶ የዐቅዱ አባል ያልነበሩ ሠራተኞችን በመመዝገብና የጡረታ መዋጮ በማስከፈል፣ የሕግ አስገዳጅነት እና የመዋጮ አሰባሰብ ሥርዓት ከግብር ክሊራንስ እና ባንክ ብድር ጥያቄ ጋር የሚያስተሳስር ሥርዓት በመፍጠርና በዲስትሪክት እና ቅ/ጽቤቶች ጤናማ የሥራ ውድድር እንዲፈጠር ቅስቀሳ በማድረግ ጭምር ብር 28.7 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ አፈፃፀሙም 112 በመቶ ነው፡፡ በ2015 ከነበረው 21.3 ብር የመሰብሰብ አፈጻጸም አንፃር የ 7,372,379,446

ብር እና 34 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ፡፡

የድርጅቶች የጡረታ መዋጮ ኦዲት ሥራን በሚመለከት 13,496 ድርጅቶችን ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ 10,963 ድርጅቶች ኦዲት ተደርገዋል፡፡ አፈጻጸሙ 81 በመቶ ነው፡፡ አዲሱን የኦዲት አደረጃጀት በሚገባ ወደ መሬት አውርዶ ወደ ሥራ እስከሚገባ ድረስ በነበረው መጓተት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት ባለመቻሉ እና በድርጅቶች የኦዲት አመራረጥ ላይ ሁሉንም ዓይነት የሠራተኛ መጠን ያላቸውን ድርጅቶች አደባልቆ ከመሥራት አኳያ ከፍተት መኖሩ የተፈለገውን ደረጃ ማድረስ ባይቻልም ካለፉት ዓመታት ዓይን የተሻለ የድርጅት ኦዲት አፈፃፀም መኖሩ ታይቷል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ብር 861,104,035 በኦዲት የተገኘ ሲሆን፣ ከተገኘው ውስጥ ብር 607,447,764 (71 በመቶ) ተሰብስቧል፡፡ የተገኘው የኦዲት ግኝት ሙሉ ለሙሉ መሰብሰብ ያልተቻለበት ምክንያት በፀጥታ ችግር፣ በድርጅቶች የባንክ ሂሳብ ላይ በቂ ገንዘብ ባለመገኙቱ እና ከፊሎቹ በህግ አገልግሎት ክትትል ሂደት ላይ በመሆኑ ነው፡፡

 

ከዚህ በተያያዘ አሰሪ ድርጅቶች ግዴታቸውን በወቅቱና በአግባቡ ባለመወጣቸው ምክንያት በሕግ አስገዳጅነት የተሰበሰበ ገንዘብን በሚመለከት አስተዳደሩ ስለአሠራሩና ስለማህበራዊ ዋስትና አፈፃፀም ግንዛቤ ከማስረፅ ሥራ በተጓዳኝ የሕግ አግባብን በመከተል የጡረታ መዋጮ ገቢ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረት የሚጠበቅባቸውን የጡረታ መዋጮ ባልከፈሉ የግል ድርጅቶች ዉዝፍ የጡረታ መዋጮ ከባንክ ሂሳባቸው ተቀንሶ ለጡረታ ፈንዱ አካዉንት ገቢ እንዲሆን ብር 519,810,497 ተጠይቆ ብር 498,814,527 ወደ ጡረታ ፈንዱ ገቢ ተደርጓል፡፡ አፈፃፀሙ 96 በመቶ ነው፡፡

የኢንቨስትመንት ሥራን አስመልክቶ የጡረታ ፈንዱን ኢንቨስትመንት ላይ በማዋልና ትርፍ በማግኘት አስተማማኝነቱንና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ሌላው የአስተዳደሩ ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢንቨስትመንት ላይ መዋል የሚገባው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ኢንቨስት የተደረገ ሲሆን፣ ብር 9.5 ቢሊዮን ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ ብር 9.75 ቢሊዮን የኢንፈስትመንት ትርፍ ተገኝቷል፡፡ ትርፉ የተገኘባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች፤ ከትሬዠሪ ቢል ብር 6,719,896,410፣ ከመንግስት ቦንድ ብር 2,505,650,000፣ ከልማት ባንክ ቦንድ ብር 327,662,877፣ ከሕንጻ ኪራይ ብር 5,887,279፣ ከጊዜ ገደብ የባንክ ተቀማጭ ብር 187,890,411 እና ከሁለት ወራት የአበል ከፍያ የቁጠባ ተቀማጭ ወለድ ብር 6,903,294 ነው፡፡ አፈጻጸሙ 102 በመቶ ነው፡፡

በዐቅዱ ተሸፍነው የነበሩ እና ዕድሜያቸው ለጡረታ በመድረሱ ማስረጃ አሟልተው ለተገኙ እና በተለያየ ምክንያት የመብት ተጠቃሚ ለሆኑ ዜጎች የጡረታ አበል ውሳኔና ክፍያን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ (ወንድ 4,151 እና ሴት 2,149) በድምሩ 6,300 ባለመብቶች ውሳኔና ክፍያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የ2016 በጀት ዓመትን የጡረታ አበል ክፍያ ማሻሻያ በመደረጉ በባለመብቱ ላይ ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩና በጡረታ አበል ክፍያ ማሻሻያው  ምክንያት አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ይከፍል ከነበረው ውጭ ለዜጎች የጡረታ መዋጮ ክፍያ ብር 398,484,272 ተጨማሪ ወጪ ተደርጎ መከፈሉ ካለፈው ዓመት ለየት አድርጎታል፡፡

Leave Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *